ደስታችሁ ታላቅ እንዲሆን የክርስቶስ መከራ ተካፋዮች በመሆናችሁ ደስ ይበላችሁ

Girma Bekele, PhD
6 min readOct 9, 2023
የኢየሱስ ሕይወት በሰውነታችን እንዲገለጥ፣ የኢየሱስን ሞት ዘወትር በሰውነታችን ተሸክመን እንዞራለን

ወርሃ ጥቅምት አድናቆትና ምስጋና ለአገልጋዮች የሚቀርብበት ወቅት ነው። ብዙ ዋጋ እየከፈላችሁ በቅንነት፣ በትጋትና በታማኝነት ለምታገለግሉ ሁሉ፣ እናመስግናለን። ከመጠነኛ እርማት ጋር በድጋሚ የቀረበው ይህ ጽሑፍ፣ እናንተን በማሰብና በመባረክ ነው። ዋጋችሁ ታላቅ ነው። ቡሩክ ሁኑ!

“በሲቃ ከማልቀስ በስተቀር ሕመሜ መታገሥ ከምችለው በላይ ሆኖብኝ በምሰቃይበት በአንድ ወቅት፣ ከጌታ ጋር ብቻ መሆን እንድችል በአጠገቤ የነበሩት ወገኖች ከክፍሌ እዲወጡልኝ ጠይቅዃቸው። ወዲያውኑ በልዑል እግዚአብሔር ፊት እንዲህ በማለት ልቤን ከእንባ ጋር አፈሰስሁኝ፦

‘አንተ አባቴ ነኽ፤ እኔም ልጅህ ነኝ። አንተ እንደ መልካም አባት ሩኅሩኅና ቸር ነህ። መከራዬ መረዳት አልቻልሁም። ሆኖም በተመሳሳይ መከራ ልጄ ሲሰቃይ ባየው፣ እንደ ወላጅ አባት እያየሁ ዝም ማለት አልችልም ነበር። ይልቁንም ዕቅፍ አድርጌው አጽናናዋለሁ፤ ከመከራውም ሁሉ እንዲያርፍ የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ። ታዲያ አባቴ እግዚአብሔር ሆይ፤ ፊትህን ከእኔ ለምን ትሰውራለህ? እጅህንስ ለምን ታከብድብኛለህ? ፊትህን በመልካምነትህስ ወደ እኔ አትመልስምን?’”

ስፐርጀን ይቀጥላል፦

“እናም ይህን ስቅዩ ልቤን በእግዚአብሔር ፊት ካፈሰስሁ በኋላ፣ ውስጤን ሰላም ሞላው። ወገኖች ተመልሰው ወደ ክፍሌ ሲገቡ፣ ‘እግዚአብሔር የጭነቅት ጩኸቴን ሰምቶአል፤ ሕመሜም ቀሊል ሆኖአል። እግዚአብሔርን እባረካለሁ’ አልኋችው።” (C. H. Spurgeon, Heaven’s Nurse Children, Metropolitan Tabernacle, Newington)

በመንፈስ ቅዱስ ኀይል የቃሉን ብርሃን በሚገልጠው ስብከተ ወንጌሉ እስከ ዛሬ ድረስ የሚወሳው እንግሊዛዊው ቻርልስ ሀደን ስፐርጀን (19 June 1834–31 January 1892)፣ አገልግሎቱ በብዙ መከራና የልብ ስብራት የታሸ ነበር። ከመርዛም ስም ማጠልሽት፤ ዐጥነት ከሚሰብር ትችት፤ ከልዝብተኛ ጋዜጠኞች የማያቋርጥ አቃቂር፤ ከአስቸጋሪ መሪዎች ጋር ማገልገል፤ ምንም ቢደረግላቸው ከማይረኩ አባላት ክፉ አንደበት፤ በቅርብ ወዳጆች ከመከዳት፤ እንዲሁም ምክንያት ከሌለው ድባቴ (causeless depression) ጋር እየታገለ ነበር የሚያገለግለው።

በስኬትና ድል መካከል ስለሚያልፈበት ነውጥ ደግሞ እንዲህ ይላል፦

“ዛሬ ሆሳዕና በማለት ስሜን ያገነነው ያው ሕዝብ፣ ሊሰቅለኝ . . . ያመንሁት ሲከዳኝ፣ እጁን የሰጠኝ ሲነሣኝ፣ በእጅጉ ያማል። ከልብ ስብራት የተነሣ፣ ከቅንድቤ ላብ እስኪንቆረቆር ድረስ ብዙ ጊዜ የስም ጉድፈት ዶፍ ወርዶብኛል፤ በጥልቅ ሐዘን የተሰበረው ልቤ ለመቆም ዐቅም አሳጦቶ ብዙ ጊዜ አንበርክኮኛል። በእግዚአብሔርም ፊት ተደፍቼ አልቅሼአለሁ። እነዚህን ነውጦች መታገሥ የምችልበት የእግዚአብሔር ጸጋ አልተለየኝም። ከሁሉም በላይ የሚከብደኝ ጌታ ፊቱን ያዞረና ዝም ያለኝ ሲመስለኝ የሚከበኝ የቀን ጨለማ ነው። ሆኖም በመከራ ብዛት የእኔ ብርታት ሲሟጠጥና የጌታ ጸጋ ሲትረፈርፍ፤ አንዲሁም በብቸኝነት ቁር ውስጥ የእርሱ አብሮነት ዐቅም ሲሆነኝ ብዙ ጊዜ አይቻለሁ . . . ። (Salvation of the Lord, Jonah 2:9 — May 10, 1857, New Park Street Pulpit Volume 3).

በቅንነት ያገለገለበት የመጥምቃውያን ማኅበር ያለ ፍትሕና ስለንጽሕናው መሟገት እንዳይችል በማድረግ በአደባባይ አዋርዶ ሲያሰናብተው፣ አገልግሎቱ አንዴ በዝና ተራራ ላይ ከፍ ሲያደርገው፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ መውጫ የሌለው የውርደትና የስብራት ሸለቆ ውስጥ ሲከተው፣ በእግዚአብሔር ሉዓላዊነት ላይ የነበረው ሙሉ እምነትና ለክርስቶስ የነበረው ፍቅር ዐቅም ሆነውታል።

በአገልግሎቱ ማብቂያ ገደማ፣ ሁለት የተቀናጁ ሴራዎች እጅግ ጐድተውት ነበር። አንደኛው፣ “The Down-Grade Controversy of 1887–88 ” (የዝቅታ ወይም የቁልቁሎሽ ውዝግብ) በመባል የሚታወቀው ሁለት ዓመት የፈጀና ሥጋዊነት የለበሰ የመጥምቃውያን ማኅበር አድካሚ ስብሰባ ነበር። ወቅቱ የቻርልስ ዳርዊን ሳይንሳዊ ፍልስፍና ለልዝብ/ልቅ ነገር መለኮት (theological liberalism) ዘር በመሆን፣ የወንጌላውያኑን መሠረታዊ የእምነት ፋይዳዎች መሸርሸር የጀመረበት ነበር። በተለይም ሁለት ዐበይት ክርስቲያናዊ እውነቶችን ፈተና ውስጥ ነበሩ። አንደኛው፣ የመጸሕፍ ቅዱስን የበለይነት፣ ሕጸጽና (infallible) ግድፈት አልባነት (inerrant) በተመለከተ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የወልድን መለኮታዊነት እንዲሁም ምትክ ቤዛዊ ሞቱን በተመለተ ነበር። ስፐርጀን የነበረውን ስጋት በግልጽ ተናግሮ ነበር። ከዚያም አልፎ፣ ውዝግቡ እርሱ በሚመራ ወርሃዊ መጽሔት ላይ በመታተሙ፣ ወደ ልቅ ነገር መለኮት ማዘንበል በጀመሩና ቀደም ሲለም ከእርሱ ጋር የሻከረ ግኑኙነት ከነበራቸው መሪዎች ጋር የከረረ ግጭት ውስጥ ከትቶታል።

ሁለተኛው ደግሞ፣ “የባሪያን ንግድና አሳዳሪነት” አስመልክቶ የነበረውን አቋም ፓለቲካዊ ይዘት እንደነበረው ተደርጐ የተነዛው የሐሰት ውንጀላ ነበር። ከዚህም የተነሣ ስብከተ ወንጌሎቹ በምድረ አሜሪካ እንዳይሰራጩ፣ እንዲሁም ተደማጭነት እንዳይኖራቸው፣ በደቡባዊ መጥምቃውያን ማኅበር ውስጥ የስም የማጥፋትና የአቅላይነት ዘመቻ ይካሄደበት ነበር።

የልቅ ነገር መለኮትን መብቀልና የሥነ-ምግባር ዝቅጠትን በተመለከተ፣ የነበረውን ሐዘን እንዲህ በማለት ገልጾአል፦

“የከተማችን ለንደን መንገዶች በበደልና በክፋት ተሞልተዋል፤ ብቅ ማለት ለጀመረው እምነት የሌሽነት እያሳየን ያለው ዝምታ (ባይተዋርነት) ያሳስበኛል. . . ያልተቀደሰች ቤተ ክርስቲያንን እግዚአብሔር ፈጽሞውኑ መኖርያው አያደርግም፤ በሥጋዊነት የተዥጐረጐረን ሕይወት እግዚአብሔር ይጸየፋል።” (The Best War-Cry, March 4, 1883)።

“የባሪያን ንግድና አሳዳሪነት” አስመልክቶ ደግሞ፣ “ከውስጥ ነፍሴ እጅግ አብዝቼ የምጠላው ነው . . . ከተለያየ እምነት ለሚመጡ [ክርስቲያኖች] የጌታን ራት አካፍያለሁ፤ ኾኖም ከባርያ ነጋጅና አሳዳሪ ጋር ፈጽሞውን ምንም ዐይነት ኅብረት አይኖረኝም።” በማለት በወቅቱ የነበረውን መዋቅራዊ ዘረኝነት ፊት ለፊት ተጋፍጧል። (The Christian Watchman and Reflector, Boston Baptist Newspaper, January 26, 1860)

በመጨረሻም በአደባባይ፣ የቤተ ክርስቲያንን ኅብረት እንደማይወድና እንደማይታዘዝ ተቆጥሮ ከኅብረቱ እንዲሰናበት ተደርጐአል። መገለል፣ የቅርቤ ናቸው ያላቸው ወዳጆቹን ማጣት፣ ብቸኝነቱና የስም ማጥፋቱ ዘመቻ ውስጡን እጅግ ጐድተውታል። በዚህ ሁሉ አስቸጋሪ የአገልግሎት ውጣ ውረድ ውስጥ እምነቱ ጽኑ ነበር፤ “To pursue union at the expense of truth is treason to the Lord Jesus . . . He is our Master and Lord, and we will keep his words: to tamper with his doctrine would be to be traitors to himself.” (እውነትን መስዋዕት ያደረገ የአንድነት ፍለጋ፣ ክርስቶስን መካድ ነው . . . እርሱ መምህራችንና ጌታችን ነው፤ ቃሉን እንጠብቃለን፤ የእርሱን አስተምህሮ መነካካት እርሱን እራሱን መካድ ነው።” (“A Fragment Upon the Down-Grade Controversy, Sword and Trowel, November 1887)

ስለመገፋቱ ደግሞ፦

“ስሜ ከጠፋው በላይ፣ ሰዎች ሊናገሩ የሚችሉት ሌላ የከፋ ማጠልሽት የለም። ከራስ እስከ እግር ጥፍሬ ድረስ፣ ተወግጃለሁ፤ እስከ ጥግ ድረስ ያልሆኑትን ምስል ተሰጥቶኛል። መልካምነቴን በተመለከት፣ አሁን መልከ ጥፉ ከተደረገበት ባላይ፣ የከፋ ማደረግ ማንም አይችልም። መጥፋት የሚችለውን ያኽል ጠፍቶአልና። ያልተጐዳ ምንም የቀረኝ ማንነት የለም።” (An All-Around Ministry Addresses to Ministers and Students, 1872, 159)

በእነዚህ ነውጦች ሁሉ መካከል፣ “የነፍስ ድቅድቅ የጨለማ ምሽት” በማለት በሚጠራውና አልፎ አልፎ በሚነሣ ሰበብ የለሽ ድባቴም ይቸገር ነበር። በአንድ ስብከቱ መካከል፣ የደባቴውን ክብደት እንዲህ በማለት ገልጾታል፦ “ባለፈው ሳምንት በሶፋ ላይ ገደም ባልሁበት፣ ድባቴ ድንገት መጣና ልቤን አወረደው። ለሰዓታት እንደ ሕፃን ልጅ አለቀስሁ፤ ምክንያቱን ግን አልውቀውም ነበር።” (The Christian’s Heaviness and Rejoicing: 1 Peter 1:6, November 7, 1858)። ጋውት (Gout) የተሰኘው የጣቶችና (በተለይም የእግር አውራ ጣት) የመገጣጠሚያዎች ቁርጥማት (አርትራይተስ) እና የኩላሊት ሕመም፣ መከራውን ቀላል አላደረጉለትም። የጋውት ድንገተኛ ጥቃት ሲመጣ የሚሰማው ስለታም የሕመም ስሜት፣ አውራ ጣትን በመዶሻ የማድቀቅ ያኽል ነው።

ከማሕፀን ሕምም ጋር በተየያዘ ምክንያተ በተካሄደ ያለተሳካ ቀዶ ጥገና፣ ለ 27 ዓመታት ከወገብዋ በታች ሽባ የነበረችውን ባለቤቱን ሱዛናናን ያስታምም ነበር። የመጨረሻዎቹ ጥቂት ዓመታቶቹ፣ የደስታ አልነበሩም። ልቡ ወድቆ ነበር። ቀድሞ በሞት የተለያት ባለቤቱ፣ “ለእምነቱ የነበረው ተጋድሎ፣ ሕይወቱን አስከፍሎታል” በማለት መስክራለታለች።

ነብዩ ኤልያስ “እግዚአብሔር ሆይ፤ በቅቶኛል፤ እኔ ከቀደሙት አባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰዳት” በማለት የጸለየበት ምክንያት ይኽው የልብ መውደቅ ነበር።

በብዙ መከራ ውስጥ፣ በትችት፣ በመገፋት ወይም ርኅራኄ በሌላቸውና በሥጋውያን አስቸጋሪ መሪዎች ጫና ሥር የሚያገለግሉ ብዙ የጌታ ባሪያዎች አሉ። አብዛኛዎቹን ሚዲያው አያውቃቸውም። በዚያ ላይ ቤት ኪራይ በመክፈልና ልጅን በማሳከም፤ አስቤዛ በማድረግና ለልጆች ትምህርት ቤት በመክፈል፤ መድሃኒት ለራሳችው በመግዛትና ታማሚ ባለቤታቸው በማሳከምና በመሳሰሉ አስከፊ የኑሮ ምርጫ አጣብቂኝ ውስጥ እያለፉ፣ በየሰንበቱ በታማኝት የሚያገለገሉ ባሪያዎች አሉ። በአንድ በሌላም መንገድ፣ በአገልግሎት ጉዞ ውስጥ፣ “ዮሴፍን የሚሸጡ ወንድሞች፣ በሙሴ ላይ የሚነሱ ማሪያሞችና አሮኖች፣ ዳዊትን የሚያሳደዱ ሳዖሎች፣ ክርስቶስን አሳልፈው እንደሰጡት ያሉ ደቀመዛሙርት፣ ጴጥሮሶችና ይሁዳዎች፣ ዴማሶች፣ አንጥረኞቹ እስክንድሮሶች፣ ሌሎቹ” አይጥፉም። በአገልግሎት ውጣ ውረድ ውስድ፣ ቅዱስ ቃሉ ሁሉ የጠራችሁ እርሱ የታመነ ነው እንደሚል፣ እግዚአብሔር ታማኝና ሉዓላዊ ነው።

እጅግ በከበደ መልኩ ሐዋርያት በመከራ ስለ ታጀበው የወንጌል አገልግሎታቸው ብዙ ጊዜ በምስጋና ልብ ተናገረዋል። በዚህ ዐውድ ሁለቱን መጥቀስ አግባብነት አለው፤

“ከየአቅጣጫው ብንገፋም አንንኰታኰትም፤ ግራ ብንጋባም ተስፋ አንቈርጥም፤ ብንሰደድም ተጥለን አንቀርም፤ መትተው ቢጥሉንም አንጠፋም። የኢየሱስ ሕይወት በሰውነታችን እንዲገለጥ፣ የኢየሱስን ሞት ዘወትር በሰውነታችን ተሸክመን እንዞራለን። የኢየሱስ ሕይወት ሟች በሆነው ሥጋችን እንዲገለጥ፣ እኛ ሕያዋን የሆንን ሁል ጊዜ ስለ ኢየሱስ ለሞት ዐልፈን እንሰጣለንና። እንግዲህ ሞት በእኛ ይሠራል፤ ሕይወት ግን በእናንተ።” (2 ቆሮንቶስ 4:8–12)

“ወዳጆች ሆይ፤ እንደ እሳት የሚፈትን ብርቱ መከራ በመቀበላችሁ እንግዳ ነገር እንደ ደረሰባችሁ በመቍጠር አትደነቁ፤ ነገር ግን ክብሩ በሚገለጥበት ጊዜ ደስታችሁ ታላቅ እንዲሆን የክርስቶስ መከራ ተካፋዮች በመሆናችሁ ደስ ይበላችሁ . . . ስለዚህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መከራ የሚቀበሉ ሁሉ ነፍሳቸውን ለታመነ ፈጣሪ ዐደራ ሰጥተው መልካም ማድረጋቸውን ይቀጥሉ።” (1 ጴጥሮስ 4:12–19)

አገልግሎት “ሙያ” ያልሆነበት ቀዳማዊ ምክንያት ከልብ ጋር የተቆራኘ በመሆኑ ነው። በፍትሕ የለሽ በደልና ስብራት የቈሰለ ልብን ተሸክሞ፣ በታማኝነትና በመሰጠት ማገልገል ትልቅ ጽናትና ጸጋ ይጠይቃል። ስፐርጀን እንዳለው፣ “አገልግሎታችን ከአእምሮ ሥራ በላይ ነው። የልብ ጉዳይ ነው፤ የነፍስ ውስጠኛ ትጋት።” (Spurgeon, Lectures to My Students, [Zondervan Publishing House, 1972], 156).

በተሰበረ ልብ እንዴት በሙሉ ኀይልና መሰጠት ለቅዱስ ቃሉ ታማኝ በመሆን ማገልገል ይቻላል? ስፐርጀን እንዳለው፣ “ለራስ በመሞት በእግዚአብሔር ሉዓላዊነትና ጸጋ በመደገፍ ብቻ ነው።” በእግዚአብሔር ሉዓላዊነት የነበረው ጽኑ እምነት፣ በልቡ የፈሰሰው ወሰን የለሽና ሁሉን አስጣይ የክርስቶስ ፍቅር፣ በጌታ ጸጋ ተደጋፊነት፣ የጸሎት ትጋቱን፣ ብቻውን ቢቀርም እንኳን ለወንጌል ንጽሕና የነበረው ቀናዒነት፣ ዐቅሙ ነበሩ።

“በብዙ [መከራ] በጌታ አገልግሎት ብንዝልና ያለ ዕድሜያችን ብንሞት፣ ክብር ለግዚአብሔር ይሁን። ምድር ትንሽ፣ ሰማይ ደግሞ ብዙ ይኖረናል ማለት ነው።” (An All Round Ministry, 126–127).

ባለቤቱ ሱዛና እንደ መሰከረችለት፦

“አንዳንድ ጊዜ, ለዓመታት የጌታ ቃል ሲያጠና፣ ሲያስብና ሲጽልይ የነበረበት የጥናት ክፍሉ እገባና በወንበሩ ሥር እንበረከካለሁ። የእጅ መደገፊያው ላይ ራሴን አሳርፍና የልቤን ጥልቅ ሐዘን በእንባ አያፈሰስሁ ብቸኝነቴን ለጌታ አጫውተዋለሁ። የእግዚአብሔርን ክብር ያስተናገደው ያው ክፍል አሁንም በዚያው ክብርና ቅድስና እንደተሞላ ውስጤን ይሰማዋል። በርግጥ ባሌ ሁሉን በመልካም የጨረሰ ታማኝ ባሪይ ነበር።”

ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን።

--

--

Girma Bekele, PhD

A consultant in Christian Mission Studies and Visiting Professor of Missional Leadership in Postmodern World Tyndale University College & Seminary, Toronto