“ዛሬ የምሰጥህን እነዚህን ትእዛዞች በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስጠናቸው” (ዘዳግም‬ ‭6‬:‭6‬‬)

Girma Bekele, PhD
4 min readJul 2, 2023
“ዛሬ የምሰጥህን እነዚህን ትእዛዞች በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስጠናቸው” (ዘዳግም‬ ‭6‬:‭6‬‬)

“ልጆቻችን ለትምህርት ወደ ቄሳር ሰድደን፣ ሮማዊ ሆነው ቢመለሱ ልንደነቅ አይገባም።” Voddie Baucham, Family Driven Faith: Doing What It Takes to Raise Sons and Daughters Who Walk with God (Good News Publishers/Crossway Books. Kindle Edition, pp. 201–202)

ነውሩ በአደባባይ ሕጋዊ ፈቃድ አግኝቶ በሚከበርበት፣ ክብሩ “እንደ ነውር” በሕግ ተከልክሎ በሚሰደድበት አስጨናቂ ዘመን ውስጥ ነው የምንኖረው። ዐመፀኛና ፈሪሓ እግዚአብሔር በራቀው ማኅብረ ሰብ መካከል ልጆቻችንን እንዴት እናሳድግ? በዚህ ክርስቶስን በገፋና የወንጌልን እውነት በረገጠ ትውልድ መካከል ልጆቻችንን እንዴት በጽድቅ መንገድ እንምራቸው? እንደማንኛውም አባት ይህ ጸጋ የሚስፈልገው የየዕለት ትግሌ ነው።

የዓለማዊነትን ፈተናዎች እንዲሁም በቤተ ሰብ ዕሴት ላይ እጅግ በከረረ ጽንፈኝነት የተነሡትን የግብረ ሰዶማዊነት ጫናዎች እንዴት እንወጣቸዋለን? በአጭሩ፣ በእግዚአብሔር ጸጋ፣ በእርሱ ጽኑ ታማኝነትና በቅዱስ ቃሉ እውነት ብቻ ነው። ስለ ልጆች፣ እኔም አብሬ ከእናንተ ጋር አብሬ ተጋዳይ አባት ነኝ። ትንሽ እግዛ ያደርጋል በሚል ዐሳብ የሚከተለውን የምክር ቃል ከጸሎት ጋር አካፍላለሁ። ከትላንትና በስቲያ ላቀረብሁት ጽሕፍ መደምደሚያ ነው።

1) ልጆቻችን ክርስቶስን በግል እንዲያውቁት፣ አዳኝና ጌታ አድረገው ሁልጊዜ በልባቸው ላይ እንዲያነገሡት ምስክር የመሆንና የመረዳት ዐደራ አለብን፤ የዘላለማዊ ሞትና ሕይወት ጕዳይ ነውና! በየዕለቱ ቅዱስ ቃሉን አብረናቸው አናንብብ፤ እንጸልይ፤ በቃልና በተግባር የእግዚአብሔራዊነት ምሳሌ እንሁንላቸው።

“ዛሬ የምሰጥህን እነዚህን ትእዛዞች በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስጠናቸው፤ በቤትህ ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛና ስትነሣም ስለ እነርሱ ተናገር። በእጅህ ላይ ምልክት አድርገህ እሰራቸው፤ በግንባርህም ላይ ይሁኑ። በቤትህ መቃኖች በግቢህም በሮች ላይ ጻፋቸው።” (ዘዳግም‬ ‭6‬:‭6‬-‭9‬)

2) ልጆቻችን በእግዚአብሔር በዘላለማዊ ዕቅዱ ውብና ድንቅ ሆነው መፈጠራቸውን በቃልና በተግባር አናሳይ፤ በተገኘውም አጋጣሚ ሁሉ ጾታቸውን በደስታ አጽንዖት አናረጋግጥላቸው።

“አንተ ውስጣዊ ሰውነቴን ፈጥረሃልና፤ በእናቴም ማሕፀን ውስጥ አበጃጅተህ ሠራኸኝ። ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፤ ነፍሴም ይህን በውል ተረድታለች።” (‭‭መዝሙር‬ 139‬:‭13‬-‭14‬)

3) እግዚአብሔር ሰውን በመልኩና በአምሳያው ወንድና ሴት ብቻ አድርጐ መፍጠሩን፤ የጋብቻና የቤተ ሰብም መሠረት ይህ ዘላለማዊና ጊዜ የማይሽረው እውነት መሆኑን በየጊዜው ልጆቻችንን እንስገንዝብ።

“እግዚአብሔር ሰውን ፈጠረ። “ስለዚህ እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጐ ፈጠራቸው። እግዚአብሔርም፣ ‘ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም፤ የባሕርን ዓሦች፣ የሰማይን ወፎች፣ እንዲሁም በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ ግዟቸው’ ብሎ ባረካቸው።” (ዘፍ 1፥27–28)።

4) ጋብቻ የተቀደሰ፣ በወንድና በሴት መካከል ብቻ የሚፈጸም እንዲሁም ከጋብቻ ውጭ ያለ ወሲብ ኀጢአት መሆኑን በተገኘው አጋጣሚ በሙሉ እናሳስባቸው። ልጅነታችው ጀምሮ ዕድሜአቸው ለትዳር ሲደርስ ትክክለኛውን ሰው እግዚአብሔር እንዲሰጣቸው መጸለይ እንዳለባቸው አናሳስባቸው፤ አብራናቸውም እንጸልይ።

“ስለዚህ ሰው ከአባቱና ከእናቱ ተለይቶ ከሚስቱ ጋር ይጣመራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።” (‭‭ዘፍጥረት‬ ‭2‬:‭24)

“ነገር ግን በፍጥረት መጀመሪያ እግዚአብሔር ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣመራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፤ ከእንግዲህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ያጣመረውን ማንም አይለየው።” (‭‭ማርቆስ‬ ‭10‬:‭6‬-‭9‬)

“ጋብቻ በሁሉም ዘንድ ይከበር፤ መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር በአመንዝሮችና በሴሰኞች ሁሉ ላይ ይፈርዳል።” ‭‭(ዕብራውያን‬ ‭13‬:‭4‬)

4) የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ እግዚአብሔር እንደሚጸየፈውና ፈጽሞውኑ ‭የእርሱ ፈቃድ እንዳልሆነ በተገኘው አጋጣሚ በሙሉ እናሳስባችው።

“‘ከሴት ጋር እንደሚደረገው ሁሉ ከወንድ ጋር አትተኛ፤ ይህ አስጸያፊ ነው።” (ዘሌዋውያን‬ ‭18‬:‭22‬፤ ሮሜ 1:26–28)

6) የልጆቻችችንን አስተማሪዎች በአካል አናግኝ፤ ማን እንደሆኑም እንወቅ። የሥርዐተ ትምህርቱን ንድፍ (curriculum) እንጠይቅ፤ የሚያንቡትን ወይም የሚነበብላቸው መጻሕፍት (በተለይም እስከ 6 ክፍል ያሉ) እንጠይቅ። ግብረ ሰዶምን የሚያራምድ መጸሐፍ፣ ወይም የቤት ሥራ እንዳይሰጣቸውና ምትክ አማራጭ ሥራ እንዲሰጣቸው መጠይቅ እንችላለን።

“ብረት ብረትን እንደሚስል፣ ሰውም ሌላውን ሰው እንደዚሁ ይስለዋል።” (ምሳሌ‬ ‭27‬:‭17‬)

“መንገዴን ቃኘሁ፤ አካሄዴንም ወደ ምስክርህ አቀናሁ። የክፉዎች ገመድ ተተበተበብኝ፤ እኔ ግን ሕግህን አልረሳሁም። በትእዛዞችህ አምናለሁና፣ በጎ ማስተዋልንና ዕውቀትን አስተምረኝ። ምስክርነትህን አሰላስላለሁና፣ ከአስተማሪዎቼ ሁሉ የላቀ አስተዋይ ልብ አገኘሁ። መመሪያህን ተከትዬ እሄዳለሁና፣ ከሽማግሌዎች ይልቅ አስተዋይ ሆንሁ። ቃልህን እጠብቅ ዘንድ፣ እግሬን ከክፉ መንገድ ሁሉ ከለከልሁ።”‭(መዝሙር‬ ‭119‬:‭59‬, ‭61‬, ‭66‬, ‭99‬-‭101‬)

7) ከትምህርት ቤት በጸሎትና በአጭር የጌታ ቃል እንስደዳቸው፤ ሲመለሱ ‭ውሎአቸውንና የተማሩትን እንጠይቅ፤ ማንኛውምን ጥያቄ ለመጠየቅ የሚችሉበትን ነጻነት እናመቻችላቸው። በየዕለቱ ክፉውን ዘር ከልባቸው ላይ በጌታ ቃል ምክር ልንነቅል ይገባል።

“ልጅን የሚሄድበትን መንገድ አስተምረው፤ በሚሸመግልበት ጊዜ ከዚያ ፈቀቅ አይልም።” (ምሳሌ‬ ‭22‬:‭6)‬ ‭

8) የትምህርት ቤት ጓደኞቻቸውን እንወቅ። አማራጭ የቤተ ክርስቲያን ጓደኞች እንዲያበዙ፤ ከቅዱሳን ልጆች ጋር ኅብረት እንዲያደርጉ፤ ልደታቸውንና ሌሎች ማኅራዊ ባዕላትን አብረው እንዲያከብሩ ሁኔታዎች እናመቻች።

“አትሳቱ፤ ‘መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን ጠባይ ያበላሻል።’” (‭‭1 ቆሮንቶስ‬ ‭15‬:‭33)‬

“ከማያምኑ ሰዎች ጋር አግባብ ባልሆነ መንገድ አትጠመዱ፤ ጽድቅ ከዐመፅ ጋር ምን ግንኙነት አለው? ብርሃንስ ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? ክርስቶስ ከቤልሆር ጋር ምን ስምምነት አለው? የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ኅብረት አለው?” (2 ቆሮንቶስ‬ ‭6‬:‭14‬-‭15‬)

9) ለኮምዩተር ሆነ፣ ለስልክ ብቻቸውን አንተዋቸው። በተለይም ዕድሜያቸው ከ 13 በታች የሆኑት። የቤት ሥራቸውንም ሆነ ማንኛውንም ኮምፒትዩተር የሚጠይቅ ሥራ በግልጽና ያለ የጆሮ ማዳመጫ በቤተ ሰብ ጠርጴዛ ላይ እንዲሠሩ አናድርግ። በስምምነትም የሰዓት ገድብ አናድርግ። አብረንም መጸሐፍ እናንንብ፤ እኛንም ስናነብ ይዩን። የቋንቋ ገደብ ካለብ፣ የታላልቆችን ርዳታ እንጠይቅ። አእምሮአቸው በመልካም ዐሳብና ቃል እንዲሞል ባተሌ እናድርጋቸው።

“በመጨረሻም ወንድሞች ሆይ፤ እውነት የሆነውን ሁሉ፣ ክቡር የሆነውን ሁሉ፣ ትክክል የሆነውን ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ሁሉ፣ ተወዳጅ የሆነውን ሁሉ፣ መልካም የሆነውን ሁሉ፣ በጎነት ቢሆን ወይም ምስጋና እንደ እነዚህ ስላሉት ነገሮች አስቡ።” (ፊልጵስዩስ‬ ‭4‬:‭8‬)

“ወጣትነትህን ማንም አይናቅ፤ ነገር ግን ለሚያምኑት በንግግርና በኑሮ፣ በፍቅር፣ በእምነትና በንጽሕና አርኣያ ሁንላቸው።” ‭‭(1 ጢሞቴዎስ‬ ‭4‬:‭12‬)

10) እንደ በጐ ልማድ እኛም ሆነ ልጆቻችንን ከኤልክትሮኒክስ ይልቅ የወረቀቱን መጸሐፍ ቅዱስ እናንብብ፤ እናጥና። ቤተ ክርስቲያንም ይህንን ታበረታታ።

“ጕልማሳ መንገዱን እንዴት ያነጻል? በቃልህ መሠረት በመኖር ነው። አንተን እንዳልበድል፣ ቃልህን በልቤ ሰወርሁ። አቤቱ፤ ሕግህን ምንኛ ወደድሁ! ቀኑን ሙሉ አሰላስለዋለሁ። ሕግህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው።” (‭መዝሙር‬ ‭119‬:‭9‬, ‭11‬, ‭97‬, ‭105‬)

11) ክርስትና የከፍታን የዝቅታ የሕይወት ጕዞ ነው። ለእኛም ጸጋ እንድሚያስፈልግ ሁሉ ለልጆቻችንም ብዙ ጸጋና ምሕረት እንደሚያስፈልጋቸው ልንረዳ ይገባል። እኛ የሌለንን “ፍጹምና” ከእነርሱ ልንጠብቅ አይገባም። ሲፈተኑና ሲወድቁ የመነሣት ጸጋ፤ ሲጠራጠሩ የጽናት ጸጋ፤ ሲደክሙ የብርታት ጸጋ፤ ሲኮነኑ የምሕረት ጸጋ፤ ሲፈሩና ተስፋ ሲቆረጡ ደግሞ የተስፋ ጸጋ መንገዶች ልንሆን ይገባል። ቃል ይሰብራል፤ ከአንደበታችን ለሚወጣው ቃል ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል። ቢያጠፉ፣ በጸጋና ለማቅናት እንጂ የቁጣችን ማብረጃ ቅጣት ልናሳርፍባቸው አይገባም። የፍቅርና የምሕረት አምላክ እኛን በየዕለቱ እንደሚታገሠን፣ እነርሱን ልንታገሥ ይገባልና!

“አባቶች ሆይ፤ ተስፋ እንዳይቈርጡ ልጆቻችሁን አታስመርሯቸው።” (‭ቈላስይስ‬ ‭3‬:‭21‬)

“አባቶች ሆይ፤ እናንተም ልጆቻችሁን አታስቈጧቸው፤ ነገር ግን በጌታ ምክርና ተግሣጽ አሳድጓቸው።” (ኤፌሶን‬ ‭6‬:‭4)

“ግድ የለሽ ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል፤ የጠቢብ አንደበት ግን ፈውስን ያመጣል።” (‭ምሳሌ‬ ‭12‬:‭18‬)

ጌታ ጸጋውን ያትረፍርፍልን!

አሜን!

--

--

Girma Bekele, PhD

A consultant in Christian Mission Studies and Visiting Professor of Missional Leadership in Postmodern World Tyndale University College & Seminary, Toronto