በሸክላ ሠሪው እጅ . . .

Girma Bekele, PhD
4 min readSep 26, 2023
መልሶ የመበጀቱ ተስፋ በሸክላ ሠሪው እጅ ብቻ ነበር

የአሦር ዓለም ዐቀፍ አገዛዛ ባበቢሎን መነሣት መሰርሰር በጀመረበት ጊዜ፣ ይሁዳ (የደቡቡ ክፍል) በጥልቅ መንፈሳዊ ቀውስ ውሰጥ ነበር። የታሪክን ፍሰት፣ የነገሥታትን መነሳትና መውደቅ በሉዓላዊነቱ የሚቆጣጠር ሁሉን ቻይ እግዚአብሔር፣ እስራኤል (የሰሜኑ ክፍል) ቃል ኪዳኗን በማፍረስ በኀጢአት መንገድ በመጽናቷ፣ በ 722 ዓ.ቅ.ክ ለአሦር አሳላፎ ሰጣት። የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስና በወቅቱ የነበሩት መሪዎች፣ ከእስራኤል አልተማሩም። ይልቁንም ልባቸው ከንስሓ እጅግ በራቀ መልኩ ደንድኖ ነበር።

“‘ለከዳተኛ ዪቱ እስራኤል ስለ ምንዝርናዋ ሁሉ የፍች ወረቀቷን ሰጥቼ አባረርኋት። ከሓዲዋ እኅቷ ይሁዳም ይህን አይታ እንዳልፈራች አየሁ፤ ወጥታም አመነዘረች። በቅሌቷም ምድሪቱን አረከሰች፤ ከድንጋይና ከግንድ ጋር አመነዘረች፤ ይህም ሁሉ ሆኖ ከሓዲዋ እኅቷ ይሁዳ ወደ እኔ የተመለሰችው በማስመሰል እንጂ በሙሉ ልቧ አልነበረም’ይላል እግዚአብሔር።” (ኤር. 3: 8–10)

ይሁዳ በአመራር፣ በመንፈሳዊ፣ በሞራል፣ በሥነ ምግባርና በፍትሕ ማጕድል ዝቅጠት ውስጥ ገብታ ነበር። ፈረሓ እግዚአብሔር እንደ ራቃት፣ የእርሱም ክብር እንደ ሸሻት አታስተውልም ነበር።

“የምታስደንቅና የምታስደነግጥ ነገር በምድር ላይ ሆናለች፤ ነቢያት በሐሰት ትንቢት ይናገራሉ፥ ካህናትም በእነዚህ እጅ ይገዛሉ፥ ሕዝቤም እንዲህ ያለውን ነገር ይወድዳሉ፤ በፍጻሜውስ ምን ታደርጋላችሁ?” (ኤር 5፥30–31)።

ይህ ውደቀት በአንድ ጊዜ የሆነ አይደለም። ሥር የሰደደና የቈየ መንፈሳዊ ሕመም ነበር። ቀደም ሲል በሚክያስ በኩል እግዚአብሔር ሐዘኑን ገልጦ ነበር። “አለቆችዋ በጉቦ ይፈርዳሉ፥ ካህናቶችዋም በዋጋ ያስተምራሉ፥ ነቢያቶችዋም በገንዘብ ያምዋርታሉ።” (ሚክ. 3፥11)።

እግዚአብሔር ይሁዳን በ 586 ዓ.ቅ.ክ አካባቢ ለባቢሎን መንግሥት አስከፈ የ 70 ዓመት ግዞት አሳልፎ ሰጠ። የመጨረሻው ንጉሥ ሴዴቅያስ ዐይኑ እያየ ባቢሎናውያን ልጆቹን ገደሉበት፤ ሁለት ዐይኖቹንም በማውጣት በሰንሰለት አስረው ወደ ባቢሎን ወሰዱት። የእሥራኤል ውበት የነበረውና በአንድ ወቅት ካህናት ማገልገል እስኪሳናቸው ድረሰ የእግዚአብሔርን ሀልዎት ያስተናገደው ቤተ መቅደስ፣ እንዲሁም ክብራቸው የነበረቸው ኢየሩሳሌም በእሳት ጋዩ፤ ቅጥሯቸውም ፈረሰ- ክብር ከእስራኤል ላይ ሸሸ።

የኤርምያስ ሰቆቃ፣ የኢየሩሳሌምን ዐመፅ፣ ውርደት፣ እፍረት፣ ስብራትና ሐዘን ይገልጣል።

“እግዚአብሔር መሠዊያውን ናቀ፤ መቅደሱንም ተወ፤ የቤተ መንግሥቶቿን ቅጥሮች፣ ለጠላት አሳልፎ ሰጠ፤. . . ዐይኔ በለቅሶ ደከመ፤ ነፍሴ በውስጤ ተሠቃየች፤ ልቤም በሐዘን ፈሰሰች።” (ሰቆ. 2፥7–11)።

ይሁን እንጂ፣ የግዞት ቅጣቱ ከተሐድሶ ተስፋ ጋር ነበር። “በሸክላ ሠሪው” የቀረበው ተምሳሌ ይህንን ያሳየናል። ምንም እንኳን ይሁዳ “ተሐድሶ ተስፋ” ማድረግ በማትችልበት ሁኔታ ውስጥ ራሷን ብታገኝም የእግዚአብሔር ፍርድና ምሕረት አልተለያዩም ነበር። ቅጣት አለ፤ ይሁዳ በጨካኙ ባቢሎን እጅ ትሰባበራለች፤ ትበታተናለች። ሆኖም እንደገና ትሠራላች። እግዚአብሔር በልዕለ ኀያልነቱ የቅጣቱ መሣሪያ የነበረውን ባቢሎንን፣ እንዲሁም ብዙ ነገር የተበላሸባትንና በቁጣው ሥር የወደቀችውን ይሁዳን በአንድ ጊዜ በእጁ ይዟል። በሌላ አባባል፣ በአንድ እጁ ፍርድ በሌላኛው ደግሞ ምሕረትን ይዟል። በቅጣትና በስብራት መካከል፣ የተሐድሶ ተስፋ ነበር።

“ከጭቃ ይሠራው የነበረውም ሸክላ በእጁ ላይ ተበላሸ፤ ሸክላ ሠሪውም በሚፈልገው ሌላ ቅርጽ መልሶ አበጀው።” (ኤር. 18፥5)።

በሸክላ ሠሪው እጅ የተከናወነው ሥራ፣ በዘፍጠረት ላይ እግዚአብሔር በፈጣሪነትና በፍጥረት አዳሽነት ራሱን የገለጠበትን ታሪክ ያስታውሰናል። እግዚአብሔር ለህልውናው ሰበብ የሌለው የፍጥረነት ብቸኛ መገኛ ነው። ያለ እርሱ ፍጥረትና ታሪክ ትርጕም የላቸውም። “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” (ዘፍ. 1፥1)። ሰውን ጨምሮ፣ በዐይን የሚታየውንና የማይታየውን የፈጠረው ራሱ እግዚአብሔር ነው። “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ።” (ዘፍ. 1፥1)፤ “እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) ከምድር ዐፈር ወስዶ ሰውን አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ።” (ዘፍ. 2፥7)።

በኦሪት ዘፍጥረት ላይ እንደምናየው፣ “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ።” (1÷31)። ይህን እጅግ መልካምነት፣ ሰላም [ሻሎም]፣ እረፍት እንዲሁም በሁሉ ረገድ እግዚአብሔር በመግቦቱ ለፍጥረት ሁሉ የሰጠውን ምሉዕነትና ስምረት ያበላሸው ኀጢአት ነው። አዳምና ሔዋን፣ በእግዚአብሔር ላይ ዐመፁ። የእግዚአብሔር የእጁ ሥራ ሆነው ሳሉ “እንደ እግዚአብሔር ለመሆን” በመፈለግ ከንቱ ምኞትና ባለመታዝዝ በደሉ።

በኀጢአት ምክንያት፣ በዘፍጥረት ምዕራፍ አንድና ሁለት ላይ የነበረው የፍጥረት ስምረት፣ ከእግዚአብሔር በስተቀር ማንም ሊያስታካክለው በማይችለው መልኩ ከሥር፣ ከመሠረቱ ተናውጧል። ሆኖም ሰው ከእግዚአብሔር ምሕረት፣ ተስፋና ተሐድሶ ውጭ አልወደቀም። ከዘፍጥረት ሦስት እስከ ራእይ የምንመለከተው ይህንኑ የእግዚአብሔርን የትድግና ሥራ ነው። አምላክ ሥጋ ኾነ! ክርስቶስ መሰቅል ላይ ደቀቀ፤ በእግዚአብሔርና በሰው፤ በሰውና በሰው፤ በፍጥረትና በሰው መካከል የተበላሸውን ግንኙነት ሁሉ አደሰ!

ሸክላ ሠሪው የተበላሸውን ሸክላ መልሶ ማበጀቱ ይህንን እውነት ያሳየናል። ሸካላው ተበላሸ፤ ሆኖም ብልሽቱ ከሸክላ ሠሪው መልሶ የማበጀት ፈቃድና ዐቅም በላይ አልነበረም። መልሶ የመበጀቱ ተስፋ በሸክላ ሠሪው እጅ ብቻ ነበር። ልክ እንደዚሁ፣ ብዙ ነገር ለተበላሸበት ሕዝቡ እግዚአብሔር የተሐድሶ ተስፋ ይሰጣል“የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ጭቃው በሸክላ ሠሪው እጅ እንዳለ፣ እናንተም እንዲሁ በእጄ ውስጥ ናችሁ።” (ኤር. 18:6)። የሸክላው ታሪክ አላበቃም፤ አልተዘጋምም። የእግዚአብሔር ሕዝብም ታሪክ ልክ እንዲሁ ነበር። “የእስራኤል ድንግል ሆይ፥ እንደ ገና እሠራሻለሁ አንቺም ትሠሪያለሽ፤ እንደ ገናም ከበሮሽን አንሥተሽ ከዘፋኞች ጋር ወደ ዘፈን ትወጫለሽ።” (ኤር 31፡4)።

እኛም እንደ አገር ብዙ ነገር ተበላሽቶብናል። ፈርጀ ብዙ በሆነ መንፈሳዊ ቀውስ ውስጥ አለን። እንደ ግለሰብና እንደ ቤተ ሰብ ደግሞ መልካቸውና መጠናቸው ይለያዩ እንጂ የእግዚአብሔርን የተሐድሶ እጅ የሚሹ የተበላሹ ነገሮች ይኖሩናል። እኛ በእውነት እንመለስ እንጂ፣ እግዚአብሔር የሚያድስ አምላክ ነው። ሆኖም እኛም ድርሻ አለን፡ “ስለዚህ ሁላችሁ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ መንገዳችሁንና ተግባራችሁን አቅኑ።” (ኤር. 18፥11)። ያንኑ የጥፋት መንገድ እየሄድን ተሐድሶን ተስፋ ልናደርግ አንችልም። ውድቀታችንን ካልተረዳንና ተሐድሶ እንደሚያስፈልገና ካላመንን፣ ተሐድሶ አይሆንም። መታመሙን ያልተቀበለ በሽተኛ፣ እንዴት ፈውስ ይገኝለታል?

“በእኔ ላይ የፈጸማችሁትን በደል ሁሉ ወደ ኋላ ጣሉት፤ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስ ይኑራችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ለምን ትሞታላችሁ? ማንም እንዲሞት አልሻምና፣ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ወደ እኔ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ!” (ሕዝ. 18፥31–32)።

የታሪክ ባለቤትና ጌታ የሆነው ልዑል እግዚአብሔር፣ ልክ እንደ ተናገረው፣ የ ሰባው ዓመት የግዞት መጠናነቀቂያ ዋዜማ ላይ የፋርስን ንጉሥ ቂሮስን በማስነሣት የባቢሎንን ትዕቢትና ኩራት ሰበረ። ቀደም ሲል በትዕቢትና በእብሪት የልዑል አምላክን ክንድ በንቀት የተመለከተውን የአሦር ዓለም ዐቀፋዊ ኀይል በባቢሎንን በማስነሣት እንዳዋረደው ማለት ነው! የኪዳኑን ሕዝብ ታደገው፤ ዳግመኛም አደሰው። ታሪኩ ቀጠለ፤ መሲሑም የመጣው ከዚሁ ተሐድሶ ካገኘ የተበላሸ ታሪክ ውስጥ ነው። እግዚአብሔር ስለ ቂሮስ፦ “ቂሮስን በጽድቅ አስነሥቻለሁ፤ መንገዱን ሁሉ አስተካክዬለታለሁ፤ ከተማዬን እንደ ገና ይሠራታል፤ ምርኮኞቼን ያለ ክፍያ ወይም ያለ ዋጋ፣ ነጻ ያወጣል፤” (ኢሳ. 45፥13) ሲል የተናገረውን ፈጸመ።

አቤቱ አምላክችን ሆይ፣ በምሕረትህ ብዛት መልሰህ አብጀን!

~ አሜን!

--

--

Girma Bekele, PhD

A consultant in Christian Mission Studies and Visiting Professor of Missional Leadership in Postmodern World Tyndale University College & Seminary, Toronto